ለራስህ የምትመኘውን ለሌሎች አድርግ

አንድ ባል ለሚስቱ እንዲህ አለ፦“ለረጅም ጊዜ ስላልተገናኘን ቤተሰቦቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ ናፍቀውኛል። ነገ ልጋብዛቸው ስለፈለኩ ፣ በደምብ ምሳ እንደምታዘጋጅልን ተስፋ አደርጋለሁ” 

በማግስቱ ጠዋት ባልየው ወደ ሥራ ሄዶ ምሳ ሰአት ሰዓት ላይ ወደ ቤት መጣና ለሚስቱ፡- “ምሳ አዘጋጀሽ? ቤተሰቦቼ በአንድ ሰዓት ውስጥ ይደርሳሉ።” አላት 

ሚስትየዋ፡- “አይ እኔ አላዘጋጀሁም ። ቤተሰቦችህ እንግዳ ስላልሆኑ በቤቱ ያለውን ይበላሉ” አለችው። 

ባልየው፡- “ፈጣሪ ይቅር ይበልሽ። ለምንድነው ትላንት ምግብ እንደማታዘጋጂ ያልነገርሽኝ? ከአንድ ሰአት በኋላ ይደርሳሉ ኮ፡ ምን ላድርግ?” አላት ። 

ሚስትየዋ ፦ “ጠርተህ ይቅርታ ጠይቃቸው። እንግዳ ሳይሆኑ የራስህ ቤተሰቦች ናቸው።” አለችው። 

ባልየው ተበሳጭቶ ቤቱን ለቆ ከወጣ ከትንሽ ቆይታ በኋላ የቤቱ በር ተንኳኳ። ሚስትየዋ ተነስታ በሩን ከፈተች። እና ቤተሰቦቿ፣ ወንድሞቿ፣ እህቶቿ ወደ ቤት እየገቡ መሆናቸውን ተመለከተች! 

አባቷም "ባልሽ የት ነው?" አላት 

እሷም፦ “አሁን ወጣ አለ” አለችው። 

አባቷም፦ "ትናንት ባልሽ ዛሬ ካንቺ ጋር ምሳ እንድንበላ ጋብዞን ነው የመጣነው። እንዴት እኛን ጠርቶ ይወጣል?" አላት 

ሚስትየዋ በዜናው በጣም ደነገጠች እና ግራ በመጋባት እጆቿን ማሸት ጀመረች። በቤቱ ያለው ምግብ ለቤተሰቧ የማይገባ ነገር ግን ለባሏ ቤተሰብ የሚስማማ ስለሆነ። 

ባሏን ስልክ ደውላ እንዲህ አለችው፦ “ ቤተሰቦቼ ምሳ እንደጋበዝክ ለምን አላሳወቅከኝም? እሺ አሁን በደንብ የተዘጋጀ ምግብ በቤትህ ስለሌለ ከውጭ ገዝተህ ባስቸኳይ አምጣ” አለችው 

ባልየው፡- “እኔ አሁን ከቤቴ ርቄያለሁ። ቤተሰቦችሽ እንግዳ አይደሉም፣ ያለውን አቅሪብላቸው” አላት ።

ምን ለማለት ነው?

ሌሎች ላንት እንዲያደርጉ የምትመኘውን ለሌሎች አድርግ፣ ሌሎች ባንት ላይ እንዲያደርጉ የማትመኘውን በሌሎች ላይ አታድርግ።



Post a Comment (0)
Previous Post Next Post